ሀዋሳ ከተማ
ለሀዋሳ ከተማ መፈጠር በዋናነት የሚነሳው የከተማውና የአካባቢው ተፈጥሮአዊ ልምላሜና በታላቁ የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኘው የሀዋሳ ሀይቅ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ሀዋሳ ከተማ ስያሜዋንም ያገኘችው ከዚሁ የሀዋሳ ኃይቅ ሲሆን ትረጉሙም በሲዳምኛ ቋንቋ ሰፊ ማለት እንደሆነ ይገለጻል፡፡
ሀዋሳ ከተማ የንጉሰ ነገስት አጼ ኃይለስላሴ የሎቄ ቤተመንግስት ግንባታ የ1951 ዓ.ም ምርቃትን ተከትሎ በ1952 ዓ.ም ከኢትዮጵያ እስከ ደቡብ አፍሪካ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን የሚያገናኘው አውራ ጎዳና ላይ የሀዋሳ ኃይቅን ተንተርሳ ከአዲስ አበባ በ275 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የተመሰረተች ዘመናዊ ከተማ ነች፡፡አሁን ሀዋሳ የስዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማ በመሆን ታገለግላለች፡፡
በዋናነት የቱሪዝም እና የኢንዲስትሪ ልማትን መሰረት በማድረግ የተቆረቆረች በመሆኗ ሀዋሳ ከተማ በሀገር ደረጃም ይሁን በቀጠናው በኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ያላት ሚና ጉልሕ በመሆኑ በአሁኑ ሰአት ቀዳሚ የቱሪዝም፣ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት ወዘተ… ከተማ ነች፡፡
ነባራዊ መገኛ
የሀዋሳ ከተማን በምዕራብ ሀዋሳ ሀይቅ፣ በሰሜን ኦሮሚያ ክልል፣ በምስራቅ ወንደገነት ወረዳ እና በደቡብ ሸበዲኖ ወረዳ ያዋስኑታል።
ሀዋሳ ከተማ በታላቁ የምስራቅ አፍሪካ ዋና መተላለፊያ አውራ ጎዳና ላይ በ 6055’0’’ --706’0’’ ኬክሮስ ሰሜንና በ 380 25’0’’ to 380 34’0’’ 38°28′ ኬንትሮስ ምስራቅ እንዲሁም በ1,708 ሜትር ወይም (5,604 ጫማ) ከወለል በላይ ትገኛለች፡፡
ሀዋሳ 1125 ኪ.ሜ ከኬንያ ዋና ከተማ ከናይሮቢ፣ 23 ኪ.ሜ ከሻሸመኔ ከተማ፣ 226 ኪ.ሜ ከቢሾፍቱ ከተማ፣ 225 ኪ.ሜ ከአዳማ ከተማ፣ 90 ኪ.ሜ ከዲላ ከተማ፣ 200 ኪ.ሜ ከሞጆ ከተማ እና 110 ኪ.ሜ ከዝዋይ /ባቱ/ ከተማ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡
የአየር ንብረት
የሀዋሳ ከተማ የአየር ንብረት ወይና ደጋ ሲሆን የተፈጥሮ ገጸ በረከቷ የሆነው የሀዋሳ ሀይቅ በከተማዋ በክረምትም ሆነ በበጋ ምንም አይነት ምቾት የሚነሳ ሙቀትም ሆነ ቅዝቃዜ የማይታይባት ከተማ አደርጓታል፡፡
የሀዋሳ በሐዋሳ ሀይቅ ዳርቻ ላይ ያለ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ያላት በመሆኑ ሰማዩ በአጠቃላይ የጠራ፣ ጭጋጋማ ሁኔታዎች ያልተለመዱባት፣ የሙቀት መጠኑ ቀላል እና መጠነኛ ነፋሶች የሚስተዋሉበት እና ምቹ የአየር ንብረት የሚታይባት ከተማ ነች።
የከተማዋ አማካይ አመታዊ የሙቀት መጠን ዝቅተኛው በክረምት 5°C እና ከፍተኛው በበጋ 34°C መካከል የሙቀት መጠኑ ይለያያል። አማካይ ዓመታዊ የዝናብ መጠን 933.4 ሚሜ የሚገመት ሲሆን ከተማዋ የወይና አደጋ የአየር ንብረት እንዳላት ይጠቀሳል፡፡ ሀዋሳ በአመት ሁለት ጊዜ በ'በልግ' እና 'ክረምት' ወቅቶች ዝናብ ታገኛለች።
አጠቃላይ የቆዳ ስፋት
የሀዋሣ ከተማ አጠቃላይ የቆዳ ሥፋት 157.2 ስኩየር ኪ∙ሜ የሚደርስ ሲሆን ከዚህ ውስጥ የአሁኑ የከተማው ዋነኛው አካል ያረፈበት ቦታ 50 ስኩየር ኪ.ሜ ሲሆን የተቀረው 11 የገጠር ቀበሊያትን እንደሚሸፍን ይገመታል፡፡
የህዝብ ብዛት
የሀዋሣ ከተማ እንደ ከተማ በ1952 ዓ.ም ስትቆረቆር የነበረው የህዝብ ብዛት ከ3000 እንደማይበልጥ የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ እንደ 1987 የቤቶችና ህዝብ ቆጠራ ሪፖርት መሠረት የከተማዋ ህዝብ 103‚000 እንደደረሰ የተገለጸ ሲሆን፣ የ1999 ሀገር አቀፍ የቤቶችና የህዝብ ቆጠራ ሪፖርት መሠረት ደግሞ የከተማዋ ህዝብ በ2015 ዓ.ም 525,053 እንደሆነ ተገልጿል። የ2016 ዓ.ም የሀዋሳ ከተማ ሶሽዮ ኢኮኖሚክስ መረጃ መሰረት አሁናዊ የሀዋሳ ከተማ አጠቃላይ ህዝብ ቁጥር 535,467 ሲሆን ወንድ 275,516 (51.4%) እና ሴት 259,951 (48.5%) እንደሆነ ያሳያል፡ ዓመታዊ የከተማዋ የህዝብ ቁጥር ዕድገት ምጣኔ 4.02% በከተማ 4.8% እና 2.8% በገጠራማው የከተማዋ አካባቢዎች ነው፡፡
የሀዋሳ ከተማ ህዝብ ብዛት በእድሜ ስብጥር ሲታይ ከአጠቃላዩ ህዝብ ውስጥ 65 በመቶው እድሜው ከ25 አመት በታች ሲሆን 5.5 በመቶው ደግሞ ከ50 አመት በላይ የሆነ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህ የሚያሳየው ከአጠቃላይ ህዝቡ አብዛኛው ወጣት መሆኑን ነው፡፡
አመሰራረት
የሀዋሣ ከተማ በ1952 ዓ.ም በቀዳማዊ ንጉሰ ነገስት በአፄ ኃይሌ ሥላሴ ዘመን የተመሠረተች ሲሆን አመሠራረቷ ከአካባቢው ልምላሜ ጋር ተያይዞ በዋናነት ከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻ እና የኢንዱስትሪ ማእከል ለማድረግ ታሣቢ ያደረገ እንደነበረ የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡
የከተማዋ የክትመት ዕድገት ደረጃዎች
- በ1952 ዓ.ም ከተማዋ ስትቆረቆር እንደ ትንሽ የቱሪዝም መዳረሻ ተደርጋ ቢሆንም በጊዜው ከአዲስ አበባ፣ ከሀረር፣ ከኮረም እና ከውቅሮ የመጡ ቁጥራቸው 4ዐ4 የሆኑ የቀዳማዊ ንጉሰ ነገስት አፄ ኃይለ ስላሴ ጡረተኛ ወታደሮች መኖሪያ እንድትሆን ታጨች፡፡
- በ1958 ዓ.ም የሀዋሣ ከተማ አድጋ የአቤላ ቱላ ወረዳ መቀመጫ ለመሆን በቃች፡፡
- በ1960 ዓ.ም ዕድገቷ ከፍ በማለት የሲዳሞ ክ/ሀገር ዋና ከተማ ሆና ተመረጠች፡፡
- በ1985 ዓ.ም ከተማዋ የደርግ መንግስት ውድቀትን ተከትሎ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች መቀመጫና የሲዳማ ዞን ዋና ከተማ ለመሆን በቃች፡፡
- ከሀምሌ 2012 ዓ.ም ጀምሮ የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማ በመሆን እያገለገለች ትገኛለች፡፡
የሀዋሳ አሁናዊ የከተማነት ደረጃ ሪጂዮ-ፖሊስ ሲሆን ከተማዋ 176 አባሉት ባሉት የከተማ ምክር ቤት የበላይነት በከንቲባ የሚመሩ የመንግስትን ስራ የሚሰሩ ---መምሪዎችና ---ጽ/ቤቶች አሏት፡፡ ከተማዋ በስምንት ክፍላተ ከተሞች እና በ32 ቀበሊያት የተደራጀች ሲሆን እነዚህ ክፍለከተሞች የሀዌላ ቱላ፣ ታቦር፣ አዲስ ከተማ፣ መነኸሪያ፣ ምስራቅ፣ ባህል አዳራሽ፣ ሐይቅ ዳር እና መሀል ከተማ ክ/ከተሞች ናቸው፡፡
መሰረተ ልማት፤-
የከተማዋን ልማት ለማፋጠንና የሰዎችን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ ይቻል ዘንድ ሀዋሳ ከተማ ሰፊ የመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ የምትገኝ ከተማ ነች፡፡
ስለሆነም የመንገድ ልማት በከተማዋ 100.3 ኪሎሜትር አስፋልት፣ 361.21 ኪሎሜትር የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ 208.55 የቀይ አፈር፣ 123.99 የጠጠር፣ 41.91 የእግረኛ አስፋልት፣ 43.92 የእግረኛ ቴራዞ፣ 50.32 የእግረኛ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ 3.2 የሳይክል መንገዶች፣ 21.45 የመንገድ ዳርቻ መብራቶች እንዳሉ አሁናዊ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የኮሪደር ልማት፣- የከተማዋን አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች ለማሳለጥና የዜጎችን የትራንስፖርት ፍሰቱን ዘመናዊ ለማድረግ እንዲሁም የከተማዋን ገጽታ ለማጉላትና አጠቃላይ የከተማዋን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ትልቁን ድረሻ እንደሚወስድ የተነደፈው የኮሪድር ልማት በሀዋሳ ከተማ በስፋት የተጀመረ ሲሆን በመጀመሪያው እቅድ እየተሰራ ያለው 43.98 ያህል ኪሎሜተሮችን ማለትም 14.74 የመኪና፣ 12.71 የብስክሌት እና 15.53 የእግረኛ መንገድ ይሸፍናል፡፡
ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን በሚመለከት የንጹህ የመጠጥ ውሀ አቅርቦት የከተማው ሽፋን 78.2 በመቶ እና የኃይል አቅርቦት 100% የደረሱ ናቸው፡፡
የከተማ ውስጥ ትራንስፖርቴሽን አገልግሎትን በሚመለከት በተለይ የትረፊክ አደጋንና የአየር ብክለትን ለመከላከልና ምቹ የትራንስፖርት አገልግሎት ስርአት እንዲገነባ የሚስችል ስርአት በመገንባት ዋና ዋና መንገዶችን በማስፋት የህዝብ መጓጓዥዎችን፤ የእግረኛ መንገዶችንና የሳይክል መንገዶችን ይበልጥ በመስፋፋት የከተማውን እንቅስቃሴዎች የማሳለጥ ስራዎች በስፋት እየተሰሩ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ሰአት በከተማዋ የከተማ አውቶቡሶች፣ ኪዊት ታክሲዎች፣ በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ባለሶስት እግር ባጃጆች ወዘተ… አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል፡፡
ማህበራዊ ልማቶች
በሀዋሳ ከተማ ተከታታይነትና ፈጣን እድገት ካሳዩ ዘርፎች ውስጥ የማህበራዊ ዘርፉ ከፍተኛውን ስፍራ የሚይዝ በመሆኑ ከተማዋ በሀገር ደረጃ ተቀዳሚና ትልቅ የህክምናና የትምህርትና ጥናትና ምርምር መደረሻ እንድትሆን አስችሏታል፡፡
ትምህርት
በሀዋሳ ከተማ አሁን ባለው ወቅታዊ መረጃ መሰረት የትምርት ሴክተሩ በሁሉም እርከኖችና አይነቶች በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ በመሆኑ የሀዋሳ ከተማ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ 4 ደረጃቸውን የጠበቁ የመንግሥት ኮሌጆች፣7 በተለያዩ የሙያ እና አካዳሚክ መስኮች ስልጠና የሚሰጡ የግል ኮሌጆች፣ 42 የመንግስት አፀደ ህፃናት፣123 የግል አፀደ ህፃናት፣ 42 የመንግስት አንደኛ ደረጃ፣101 የግል አንደኛ ደረጃ፣ 14 የመንግስት ሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም 18 የግል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቶች ይገኛሉ፡፡
የጤና አገልግሎት፣-
በተመሳሳይ እንደትምህርቱ መስክ ሀዋሳ ከተማ በጤና ህክምና እና የጤና ቱሪዝም ዘርፍ ብዙ ርቀት የተጓዘች ሲሆን የሀዋሳ ሪፈራል እንዲሁም በርካታ የግል ሆስፒታሎች ከፍተኛ ህክምናዎችን የሚሰጡበት ደረጃ ላይ በመድረሳቸው በየአመቱ ከበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች በብዙ ሽዎች የሚገለጹ ዜጎች ወደ ሀዋሳ ይመጣሉ፡፡ 1 ሪፈራል ሆስፒታል፣ 4 የመንግስት ትላልቅ ቅርንጫፍ ሆስፒታሎች፣ 5 የግል ሆስፒታሎች፣ 7 የጤና ማእከላት፣ 15 የጤና ኬላዎች፣ 15 የግል ክሊኒኮች፣ 46 የመድሀኒት ቤቶች፣ 2 የምርመራ ላብራቶሪዎች እና 55 ፋርማሲዎች በህክምናው ዘርፍ አገልግሎቶችን ይሠጣሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዜጎች ዘመናዊ የህክምና አገልግሎቶችን እንዲያገኙ የኦንላን የህክምና የማማከር ስራዎች እየተሰፋፉ ነው፡፡
የፋይናንስ አገልግሎቶች
በከተማው ውስጥ በርካታ የፋይናንሺያል አገልግሎቶች የሚሰጡ ተቋማት የሚገኙ ሲሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ዳሸን ባንክ፣ ልማት ባንክ፣ አንበሳ ባንክ፣ ንብ ባንክ፣ አዋሽ ባንክ፣ ሕብረት ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክ፣ ብርሃን ባንክ፣ ቡና ባንክ፣ አባይ ባንክ፣ አዲስ ባንክ፣ ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ፣ ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ እና ደቡብ-ግሎባል ባንክ፣ ሲዳማ ባንክ፣ ሲንቄ ባንክ፣ ወዘተ… እንዲሁም አነስተኛ የብድር እና የቁጠባ አገልግሎትን የሚሰጡ ተቋማትንም መጥቀስ ይቻላል፡፡
ኢንዲስትሪ እና ንግድ
ሀዋሳ በሀገሪቱ ካሉት የሸማቾች ማእከል አንዷ እና የኢንዱስትሪ እና የንግድ እንቅስቃሴዋ አስኳል ናት። በአሁኑ ጊዜ ከተማዋ የመንግስት ኮርፖሬሽኖች እና በግል ባለቤትነት የተያዙ የኢንዱስትሪ እና የንግድ ኩባንያዎች ማዕከል ሆና ታገለግላለች። ከሐዋሳ ዋና ዋና ኢንዱስትሪዎች መካከል የምግብ ማቀነባበሪያ እና የፍጆታ ዕቃዎችን (ለምሳሌ ቢራ፣ ጨርቃጨርቅ እና ጫማ) በአጠቃላይ ለውጭና ለአገር ውስጥ ገበያ የሚያመርቱና በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ናቸው። የግንባታ እና የተለያዩ የአገልግሎት ኢንዱስትሪዎችም ለከተማው ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡
ኢንቨስትመንት
በስምጥ ሸለቆ ውስጥ ከትማ ሀዋሳ ሀይቅንና የአካባቢውን ልምላሜ እንደ የኢንቨስትመንት አማራጮች በመጠቀም እና ሌሎችን የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን በመጠቀም በተለይ በሆቴል፣ በትላልቅ የገበያ ማዕከላት ግንባታ፣ በትምህርትና ጤና ዘርፍ፣ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዘርፍ፣ በሪል ስቴት፣ በቀለም ፋብሪካ፣ በቆርቆሮና ምስማር ፋብሪካ፣ በጨርቃጨርቅ፣ በሳሙና ፋብሪካ፣ በሲሚንቶ ፋብሪካ፣ በለስላሣ መጠጦች ፋብሪካ፣ በቢራ /አልኮሆል/ ፋብሪካ፣ በከተማ ግብርና… ወዘተ መሰማራትና ውጤታማ መሆን ይቻላል፡፡
በሀዋሳ ኢንቨስትመንቱን አዋጭ የሚያደርጉ ብዙ ምቹ ሁኔታዎች ያሉ ሲሆን የከተማዋ ለአዲስ አበባና ለአጐራባች ገባር ከተሞች በቅርብ ርቀት ላይ ማዕከልነቷን በጠበቀ መልኩ መገኘት ለየትኛውም አገልግሎት የሚውሉ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ከአካባቢው በስፋት መገኘት ሠፊ የገበያ ዕድል በአካባቢዉ መኖር የጠራና ባለሀብቱን ሊያሰራ የሚያስችል የኢንቨስትመንት ፖሊሲ መኖር የከተማ አስተዳደሩ ባለሀብቱን የመቀበል አቅምና መስተንግዶ የህዝቡ እንግዳ ተቀባይነት የሰው ጉልበት በበቂ ሁኔታ መገኘት የ103 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በቂ የመሰረተ ልማት የተሟላላቸው ለተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች የሚውሉ ቦታዎች መዘጋጀታቸው፣ ከ23 በላይ የፋይናንስ ስርዓቱን የሚያግዙ የገንዘብ ተቋማት መኖር በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
የከተማዋ ገቢ/ኢኮኖሚ
የሀዋሳ ከተማ ተገቢውን ልማቶቿን ለማሳካት የሚስያችሉ የተለያዩ የገቢ መሰረቶች አሏት። የከተማዋ የኢኮኖሚ መሰረቶች መካከል የአገልግሎት ዘርፉ፣ የኢንዱስትሪው ሴክተር፣ የግብርናው ዘርፍ፣ የፋይናንስ ዘርፍ፣ የቱሪዝም ሴክተሩ ወዘተ… በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ የከተማ አስተዳደሩም በህግ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ክፍያዎችን እና ታክስን ይጥላል፣ይሰበስባል፡፡
ግብር የመሰብሰብ አቅሙ የከተማዋ ማህበራዊ አገልግሎቶችን እንደ ጤና እና ትምህርት፣ ወሳኝ መሠረተ ልማቶችን እንደ ኤሌክትሪክ እና መንገድ እና ሌሎች የህዝብ እቃዎችን ፋይናንስ ለማድረግ የሚያስችል ነው። ከተማዋ ከተለያዩ ምንጮች ማለትም ከማኑፋክቸሪንግ፣ ከትራንስፖርት፣ ከሆቴልና ቱሪዝም፣ ከኮንስትራክሽን፣ ከጅምላና ችርቻሮ እና ከሌሎችም ዘርፎችም ገቢዋን ታገኛለች፡፡
ቱሪዝም
የሀዋሣ ከተማ አመሠራረት ከተማዋን የቱሪዝም መዳረሻ ከማድረግ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ የታመነ ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ሀዋሣን ሊጐበኝ ለሚመጣ የትኛውም የሀገር ውስጥም ይሁን የውጭ ቱሪስት በተለየ ሁኔታ ተዝናንቶባትና ከአይምሮው የማይጠፋ ትዝታ ሰንቆ ይመለሳል ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ የሀዋሳና የአካባቢው የተፈጥሮ ጸጋዎች፣ ዘመን ጠገብ ባህላዊና ማበራዊ መስተጋብሮች፣ ዘመናዊና ትላልቅ የሆቴሎችና የፋይናንስ አገልግሎቶች፣ የትራንስፖርት አማራጮች መኖር፣ በቂና ዘመናዊ የመሰረተ-ልማትና ማህበራዊ ልማቶች፣ ዘመናዊ የመገናኛ አውታሮች መስፋፋት፣ የከተማዋ ሰላምና የህዝቡ የእንግዳ ተቀባይነት ወዘተ… ከተማዋን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ አድርጓታል፡፡
ስፖርትና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች
የታሪክ ድርሳናት እንደሚያመለክቱት ሀዋሳ በሀገራዊ ትላልቅ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በእግር ኳስ፤ የእጅ ኳስ፣ አትሌቲክስ ዘርፎች ትላልቅና ስመጥር ክለቦችና ስፖርተኞችን በማፍራት ትልቅ ድርሻ ስታበረክት የቆየች ከተማ ናት፡፡የመንግስትን የስፖርት ልማት ፖሊሲ መሰረት በማድረግ ስፖርቱ ህዝባዊ መሰረትና ተሳትፎ እንዲኖረው የተለያዩ ማህበራት እንዲደራጁና እንዲሳተፉ በማድርግ፣ የስፖረት ማዘውተሪያዎችን በማልማትና አቅማቸውን ከፍ በማድረግ ከተማዋ ከተማዋ የትላልቅ ሀገራዊና ተሸጋሪ ውድድሮችን ማስተናገድ የምትችልና በዘርፉ ተጠቃሚ የምትሆንበት ደረጃ ላይ ደርሳለች፡
===////===