ቱሪዝም- ሀዋሳ
ከከተማዋ መቆረቀቆር ጋር ተያይዘው የተጻፉ የታሪክ መረጃዎች የከተማዋ መመሰርት አንዱ ፍላጎት ዘመናዊና ተመራጭ የቱረስት መዳረሻ ለመፍጠር እንደነበር ይነገራል፡፡ ሀዋሳ በቀጣናው ካሉ የቱሪስት መደራሻ ቦታዎች ኢንዲስትሪው የሚጠይቃቸውን ሁሉ በማሟላት በቀደምትነት የምጥጠቀስ ከተማ ነች፡፡ ሀዋሳ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ሴክተር የሚጠይቃቸውን አለምአቀፍ መለኪያዎች ማለትም መስህብ፣ ትራንስፖርት፣ እንግዳ ተቀባይነት ባህልና ልምድ፣ ድርጅታዊ ብቃት እንዲሁም የቱሪዝም መሠረተ ልማት ያሟላች ከዛም ባለፈ የራሷ ልዩነቶች ያሏት ናት፡፡ ይሕ ኢንዱስትሪ ከሁሉም በላይ ፍጹም ሰላምንና ደህንነትን የሚጠይቅ በመሆኑ ሀዋሳ ያላት ሰላም አስተማማኝ መሆን ከተማዋ በዚህ ዘርፍ ፍጹም የበላይነት እንዲኖራት ያደርጋታል፡፡ የቱሪዝም ኢንዲስትሪው ከሚመዘንባቸው ዘርፎች አኳያ የሀዋሳ ከተማ ምን ትመስላለች?
ሀ/ የቱሪዝም መስህቡ ዘርፍ፣- በዚህ ዘርፍ ሦስት ዋና ዋና መስህቦች ይጠቀሳሉ፡፡ እነሱም አንደኛው የተፈጥሮ ለምሳሌ ኃይቆችን፣ ተራሮችን፣ የአየር ንብረትን፣ የዱር እንሰሳትን፣ ወንዞችን፣ ቢቾችን ወዘተ ሲያካትት ሁለተኛው የባህል መስህብ በዘመናዊነት ያልተበከለ የአካባቢው ማህበረሰብ መገለጫ የሆኑ መንደሮችን፣ ስነምህንድስና ሥነጥበቦችን፣ አመጋብበን አለባበስን፣ እምነትን፣ ቋንቋን፣ ባህላዊ የአስተዳደር ስርአትን ወዘተ… የሚያካትት ሲሆን ሶስተኛው ልዩ መስህቦች በሰው ልጅ ለተለያዩ አገልግሎቶች የተገነቡ ለምሳሌ. ሙዚየሞች፣ የመዝናኛ ማዕከላት፣ የውሃ ገንዳዎች፣ የአትሌቲክስ ስታዲየሞች፣ የመዝናኛ ፓርኮች፣ መካነ አራዊት እና የህጻናት ማሳደጊያዎች ወዘተ… ናቸው።
የተፈጥሮ መስህቦች፤- ሀዋሳ ከተማን ለቱሪስት ተመራጭ ከሚያደርጓት አንዱ በልዩነት የሚጠቀሱት የተፈጥሮ ጸጋዎቿ ናቸው፡፡ ቀጥሎ ከብዙዎቹ ዋና ዋናዎቹን እንመለክት፡፡
የሐዋሳ ሐይቅ፣
ጎብኚ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ሀዋሳ እስኪደርስ ድረስ በዋናው መንገድ ግራና ቀኝ በተቀራራቢ ርቀት ላይ የተሰበሰቡትን 6ቱን የታላቁ ስምጥ ሸለቆ ገጸበረከቶች የሆኑትን ሻላ፣ አብያታ፣ዝዋይ፣ ላንጋኖ፣ ሰው ሰራሽ ቆቃ ሕይቅና ውብ በሆነ ከተማ የተከበበና ተፈጥሮ በቸረችው ድንቅ ገጽታው የሚታወቀውን የሐዋሳን ሐይቅ የመጎብኘት እድል ያገኛል፡፡
በ2007 በተደረገው የክልሉ ውሃ ሀብት ልማት ቢሮ ጥናት መሰረት የሐዋሳ ሀይቅ አጠቃላይ ዙሪያ ስፋት 94 ኪሎ ሜትር እስኩዌር፣ 1363 ሴንቲ ሜትር ኪዩብ የውሃ መጠን፣ 22 ሜትር ከፍተኛ ጥልቀት 13.3 ሜትር አማካይ ጥልቀት፣ ስፋቱ 8 ኪሎ ሜትር እና 16 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው፡፡
በሐዋሳ ሐይቅ ውስጥና በዙሪያው የየብሱ ክፍል ጨምሮ የተለያዩ የእጽዋት አእዋፋትና የውሃ ውስጥ እንስሳት ይገኛሉ፡፡ በተለይም አመሻሽ አካባቢ ከሐይቁ አድማስ ጫፍ የሚታየው የፀሐይ ግብአት ሐይቁ በተለየ መልኩ ተወዳጅና ሳቢ እንዲሆን ያደረገው አንዱ የተፈጥሮ ስጦታ ነው፡፡
ለከተማዋ መመስረት ምክንያት የሆነውና የከተማዋ ዋነኛ መስህብ የሆነው የሐዋሳ ሐይቅ በዙሪያው የታቦር ተራራ፣ የአሞራ ገደል ፓርክ፣ የሚሊኒየም ደን፣ የፍቅር ሀይቅ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ ሌዊ ሪዞርት፣ ሀይሌ ሪዞርት፣ ዋቢሸበሌ ሆቴሎች በዙሪያው አጅበው የተለየ ውበት አጎናጽፈውታል፡፡ በሐይቁ አካባቢ መኖሪያቸውን ያደረጉ እንደ ጋጋኖ፣ ሄረን፣ ዲንቢን፣ ንስር፣ ሺሚላ፣ ሀመርኮ፣ አባኮዳ እና ሌሎችም በሀገር ውስጥ ብቻ የሚገኙ አእዋፋት ሌላው የሀይቁ ውብ ገጽታዎች ናቸው፡፡ ሀይቁን መኖሪያቸው ያደረጉ እንደ ጉማሬ፣ አርጃኖ፣ የውሃ ውስጥ እበብ፣ እና የተለዩ ዝሪያ ያላቸው አሳዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በተለያዩ ህብረቀለማት ያጌጡ የሞተር ጀልባዎች ጎብኚዎችን ከፍቅር ሐይቅ ወደ አሞራ ገደል፣ ከሐይለ ሪዞርት ወደ ሌዊ ሪዞርት፣ ከፍቅር ሐይቅ ወደ ጣሃጎዳ ደሴት፣ ወዘተ በማዝናናት የጎብኚዎችን ቀልብ የሚገዙ የስፍራው ሁነቶች ናቸው፡፡
የታቦር ተራራ
የታቦር ተራራ የሐዋሳን ሐይቅ ካጀቧት ድንቅ ተፈጥሮ ገጽታዎች መካከል አንደኛው ነው፡፡ ከከተማው ደቡባዊ ምዕራብ አቅጣጫ ላይ የሚገኝ መጠነኛ ተራራ ሲሆን በተለያዩ የዛፍ ዝርያዎች የተሸፈነ እጅግ ማራኪ ቦታ ነው፡፡ የተራራው ዋነኛ ውበት ከስፍራው ሆነው ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች ሲመለከቱ የሚያገኙት ድንቅ ገጽታ ነው፡፡ ከስሩ የተንጣለለውን የሐዋሳ ሀይቅን፣ የአሞራ ገደል ፓርክን፣ እንዲሁም በዘመናዊ የከተሞች ምስረታ መስፈርትን ይዛ የተመሰረተችውን የሐዋሳ ከተማን ከፊል ገጽታ፤ በተራራው በስተደቡብ ጫፍ የሚገኘውን ጥልቴ ጉብታ በማየት የማይረሳ ቆይታ እንዲኖርዎት የሚያስችል ሲሆን ከዚህም ባለፈ በነዋሪዎቿ ተመራጭ የስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማዘውተሪያ ስፍራም ነው፡፡
ተራራውን በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ በጀት በመመደብ በተሻለ መልኩ ለማልማት የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን በዚህም የደረጃዎች መወጣጫና ማረፍያ ስፍራዎች ግንባታ በመፋጠን ላይ ይገኛል፡፡
የአላሙራ ተራራ
የአላሙራ ተራራ በከተማዋ በስተደቡብ ክፍል ላይ የሚገኝ ትልቁ ተራራ ነው፡፡ ይህ ተራራ የከተማዋን ሙሉ ገጽታ እንዲሁም መንደሮችንና በአካባቢው የሚገኙ ሜዳማ ስፍራዎችን ወለል አድርጎ የሚያስቃኝ ድንቅ የተፈጥሮ መስህብ ነው፡፡ ይህ ተራራ የተለያዩ የዱር እንስሳት በተለይም የጅብ ዋነኛ መኖሪያነት ሆኖ ያገለግላል፡፡ ይህ መስህብ የከተማዋን ገጽታ በተለየ መልኩ ማመላከት የሚያስችልም እንደሆነ ይታመናል፡፡
ቡርቂቱ ፍልውሃ
ከከተማዋ ደቡባዊ ምዕራብ አቅጣጫ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት በሀዌላ ቱላ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኝ ሌላው የከተማዋ ተፈጥሯዊ መስህብ ነው፡፡ ይህ ፍልውሃ በሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ዘንድ ብቻ ሳይሆን ከክልሉ ገጠራማ እና ከኦሮሚያ ክልል አከባቢዎች ህብረተሰብ ዘንድ እጅግ ተመራጭነት ያለው መስህብ ነው፡፡ ፍልውሃ እንደ ፀበልነት፣ በሽታን ለመከልከል፣ ለአጥንትና ለጡንቻ ህመሞች መፈወሻነት፣ የመተንፈሻ አካልና፣ የምግብ መፍጨት ስርዓቶችን ለማስተካከል እና ለተለያዩ የጤና እክሎችን ለማስተካከል ሲባል በቀን በአማካይ ከ1000 ሰዎች በላይ ይጎበኙታል፡፡
አሞራ ገደልና የዓሳ ገበያ፡-
በልማድ አሞራ ገደል እየተባለ የሚታወቀው የጉዱማሌ መናፈሻ ስፍራ በከተማዋ ምዕራብ አቅጣጫ በሐይቁ ዳርቻ ላይ የሚገኝ ማራኪ የመዝናኛ ቦታ ነው፡፡ አሞራ ገደል የሚለውን ስያሜ ያገኘው በአካባቢው ከሚኖሩ የተለያዩ አዕዋፋት መኖሪያ በመሆኑ መነሻነት ሲሆን እንደ ጦጣ፣ ጉሬዛ፣ ሽኮኮና የመሳሰሉት የዛፍ ተንጠልጣይ እንስሳትም በአከባቢው በብዛት ማግኘት የተለመደ ነው፡፡ ከዚህ ሥፍራ ላይ ሆኖ የሀይቁን አብዛኛው ክፍል በተሻለ ሁኔታ ለመቃኘት ያስችላል፡፡
አሳ ገበያ (fish market)፡- በከተማዋ የሚገኙ እድሜ የጠገቡ ሀገር በቀል ዛፎች በዋናነት የሚገኙት በዚህ ስፍራ ሲሆን ዘወትር ማለዳ ታታሪዎቹ አሳ አስጋሪዎች ሌሊቱን በመረባቸው ሲያጠምዱ ያደሩትን የቆሮሶ፣ ብልጫና ሌሎች ጣፋጭ የአሳ ዝርያዎች ከጣውላ በተሰሩ ጀልባዎቻቸው ጭነው ወደ ሀይቁ ዳርቻ በሚገኘው የአሳ ገበያ ስፍራ ይቀርባሉ፡፡ በአሳ አስጋሪዎች ማህበር የሚተዳደረው የዓሳ ገበያው ከኦሲስ ኢንተርናሽናል ሆቴል በ1 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከአሞራ ገደል መናፈሻ ጎን ሲገኝ በተለያየ ሳቢ እንቅስቃሴዎች የተሞላ ነው፡፡
ማልደው ቁጥራቸው በዛ ያሉ ከጣውላ የተሰሩ ጀልባዎች ሌሉትን ያጠመዱዋቸውን አሳዎችን በውስጣቸው ይዘው በሐይቁ ዳርቻ ይደረደራሉ፣ ከመረቦቻቸው እያወጡ እንደየሰው ፍላጎት በፈርጅ በፈርጁ ይለያሉ፣ ጥብስ፣ ቅቅል (ሾርባ)፣ ፊሌቶ ወዘተ አሳ የሚበልቱ ልጆች፣ ነጋዴዎች፣ አሳ ቀቃይና ጠባሾች፣ የዳቦ፣ ዓሳ ውሃ፣ ለስላሳ፣ ሶፍት ወዘተ አቅራቢዎች የጀበና ቡና ትዕይንት የአሳውን ተረፈ ምርት ለመቋደስ ከሚጠብቁት አባኮዳ፣ ቆልማሚት፣ አሳዋጭና አሳ አውጭ፣ የተራረፈ ዳቦዎችንና ቂጣዎች ቢደርሰን ብለው ግብግብ የሚፈጥሩ ጦጣዎች ተደማምሮ ለስፈረው የተለየ ውበት ያጎናጽፉታል፡፡
የዱር እንሰሳትና አእዋፋት
በሀዋሳና አካበቢያዋ በተለይ የሀዋሳ ኃይቅንና ተራራዎቹን በመኖሪያነት የሚጠቀሙ በርካታ የዱር እንስሳትና አእዋፋት ይገኛሉ፡፡ ከዱር እንሰሳቶቹ መካከል በብዛት ጦጣ፣ ጉሬዛ፣ ሽኮኮ፣ አርጃኖ፣ ጉማሬ በብዛት በተለይ በሐዋሳ ኃይቅ ውስጥና አካባቢው የሚገኙ ሲሆን ጅብና ሌሎችም የዱር እንስሳት በአላሙራ ተራራ ላይ ይገኛሉ፡፡
የውሃ ውስጥ እንስሳት: - ጉማሬው በፊል-ውሃማ ፣ በወንዞች፣ በሀይቆች እና በረግረጋማ ቦታዎች ከ 5 እስከ 30 ሴቶች እና ወጣት ሆነው የሞኖሩ ናቸው፡፡ በቀን ውስጥ በውሃ ወይም በጭቃ ውስጥ የሚቆዩ ሲሆን መራባት እና ልጅ መውለድ በውሃ ውስጥ ይከሰታሉ፡፡ ምሽት ከውሃ ውስጥ በመውጣት ሣር ለመጋጥ ይወጣሉ፡፡
ጉማሬዎች በርሜል ቅርጽ ባለው አካል፣ ግዙፍ አፍ እና ጥርሶቻቸው፣ ጸጉር በሌለው ሰውነታቸው፣ በከፍተኛ መጠን ባለው እግራቸው ይታወቃሉ። በክብደት ከነጭ አውራሪስ (1½ እስከ 3½ ቶን) እና ከነጭ አውራሪስ (1½ እስከ 3½ ቶን) በክብደት ሦስተኛው ትልቁ አጥቢ እንስሳት እንደሆን ይነገራል፡፡ ጉማሬው ከትልቁ አራት እጥፍ አንዱ ሲሆን ምንም እንኳን ቅርፁ እና አጭር እግሮች ቢኖረውም ሰውን በቀላሉ ሊያሸንፍ ይችላል። ጉማሬዎች በሰአት በ30 ኪሜ (19 ማይል በሰአት) በአጭር ርቀት መጓዝ ይችላል። ጉማሬ በዓለም ላይ ካሉት በጣም ጠበኛ ፍጥረታት አንዱ ሲሆን ብዙውን ጊዜ በአፍሪካ ውስጥ በጣም አደገኛ ከሆኑት እንስሳት አንዱ ተደርጎ ይወሰዳል።

የጉማሬ አይኖች፣ ጆሮዎች እና አፍንጫዎች በራስ ቅሉ ጣሪያ ላይ ከፍ ብለው ተቀምጠዋል። ይህም አብዛኛው ሰውነታቸው በውሃ ውስጥ ጠልቀው እንዲቆዩ እና በሐሩር ክልል በሚገኙ ወንዞች ጭቃ ውስጥ እንዲቀዘቅዙ እና የፀሐይ ቃጠሎን ለመከላከል ያስችላቸዋል። ጉማሬዎች ምሽት ላይ ውሃውን ትተው ወደ ውስጥ፣ አንዳንዴም እስከ 8 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይጓዛሉ፡፡ ጉማሬዎች በአጫጭር ሳር ቦታዎች በመሄድና በመሰማራት ከአራት እስከ አምስት ሰአት በግጦሽ ያሳልፋሉ፡፡ ጉማሬ በእያንዳንዱ ምሽት 68 ኪሎ ግራም ሳር ይበላሉ፡፡
አእዋፋት፣- በሀዋሳ ከተማና አካባቢው በርካታ አእዋፋት በቅርብ በወጣ መረጃ እስከ 80 የሚደርሱ ዝራያዎች እንደሚገኙ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ እነዚህን ውብና ድንቅ ቀለሞች ያላቸውን አእዋፋት ለመጎብኘት ከየትኛውም የአፍሪካ ክፍል የተሻለው ቦታ ሀዋሳ ስለመሆኑ ምንም ጥያቄ አይኖርም፡፡






ባህላዊ መስህቦች፣- የባህል መስህቦች በዘመናዊነት ከፍተኛ ተጽዕኖ ያልደረሰባቸው በአንድ የተወሰነ አካባቢ (ተፈጥሮአዊ አቀማመጥ) ውስጥ ያሉ የአገሬው ተወላጆች አኗኗር ዘይቤን የሚያካትቱ ከተፈጥሮ መስህቦች በሁለተኛ ደረጃዎች ላይ የሚቀመጡ መስህቦች ናቸው። የገጠር መንደር፣ ስነ-ህንፃ፣ አለባበስ፣ ጥበብ፣ የእጅ ጥበብ፣ እምነት፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ የአካባቢ ምግብ ወዘተ… በዚህ ስር የሚቀመጡ ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ሀዋሳ የብዙሀንና የቆዩ ልምዶችና አኗኗሮች ባለቤት በመሆኗ ብዙ ጉዳዮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ሀይማኖታዊና ባህላዊ በአላት
የሃዋሳ ከተማ በርካታ ሐይማኖታዊና ባህላዊ ደማቅ የአደባባይ በአላትን የምታስተናግድ ሲሆን ከነዚህም መካከል ዋና ዋናዎቹ የጥምቀት፤ የቅ/ገብርኤል የንግስ በዓል፤ የደመራ እና ፍቼ ጫምባላላ፣ የመውሊድ በአላት፣ ወዘተ... ይጠቀሳሉ፡፡
የጥምቀት በዓል
በዓመት አንድ ጊዜ በጥር ወር ላይ የሚከበር ታላቅ ሀይማኖታዊ በዓል ነው፡፡ የጥምቀት በዓል በክረስትና ኃይማኖት ተከታዎች በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣ ኢየሱሥ ክርስቶስ በ፴ ዓ.ም በፈለገ ዮርዳኖስ በመጥምቁ ዪሀንስ እጅ በዮርዳኖስ ባህር የተጠመቀበትን ዕለት የሚያታውስ ኤጲፋንያ በመባልም የሚታወቀው ደማቅ በዓል ነው፡፡
በአገራችን፣ ጥር ፲ ቀን፣ በከተራ፣ በገጠር ወራጅ ውሃ የሚከተርበት፣ ታቦታት ከየአቢያተ ክርስቲያናቱ በዓሉ ወደሚከበርበት ቦታ በምዕመናን ታጅበው እየዘመሩ ይሄዳሉ። እዚያም በየተዘጋጀው ድንኳን እንዲያርፉ ተደርጎ ሌሊቱን እዛው ያሳልፋሉ።በከተሞች ግን ሰው ሰራሽ ግድብ ይሰራል።

ጥር 11 ቀን የጥምቀት ዕለት፤ በገጠር፣ ጎኅ ሲቀድ ምእመናን እዚያው በድንኳኑ ዙሪያ አስቀድሰው ሲጨርሱ በካህናት መሪነት ሁሉም ወደከተራው ያመራና ውሃውም ተባርኮ ሕዝቡ ይረጫል። የክርስትና ስማቸውንም የረሱ ወደካህናቱ ይቀርቡና አዲስ የክርስትና ስም ይቀበላሉ። «ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ፤ ሰማያዊው በመሬታዊው እጅ ተጠመቀ» የሚለው የዕለቱ ቀለም በሊቃውንቱ አንደበት በያሬዳዊ ዜማ ጎልቶ ይሰማል። ከዚህ ሥነ ሥርዓት በኋላ በመቋሚያ፣ በከበሮና በጽናፅል በሚታጀብ ኃይማኖታዊ ዝማሬና ዘፈን፣ ወንዱ በሆታ፤ ሴቱ በእልልታ፤ ካህኑ በሃሌታ ታቦተ ሕጉን አጅበው፣ እንደያመጣጣቸው ወደየቤተክርሲያናቸው የሚመለሱ ሲሆን በተለይ በሀዋሳ በታቦት ማደሪያው በድጋሚ አድረው በተመሳሳይ ስነስርአትና አጀባ በጥር 12 ወደየቤተክርስቲያነታቸው ይመለሳሉ። ከከተራ ቀን ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት በከተማዋ ከፍተኛ ድባብ ይፈጠራል፡፡
የመስቀል ደመራ በዓል
በመስቀል ዋዜማ ላይ መስከረም 16 ላይ የሚከበር ሲሆን በዓሉ የመስቀል በዓልን ለማብሰር ችቦ የሚለኮስበት ሲሆን በኦርቶዶክስ ሀይማኖት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ሆኖ በዓሉን በርካታ የሀገር ዉስጥና የዉጭ ጎብኚዎች ይታደሙታል፡፡

የመውሊድና ኢድ አል ፈጥር በዓላት
በሙስሊሞች ዘንድ ትልቅ ቦታ ያለው የጾም ፍቺ በዓል ነው፡፡ ይህ በዓል በሀዋሳ ከተማ በአደባባይ በድምቀት የሚከበር በመሆኑ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች የሚታደሙበት ሀይማኖታዊ ክብረ በዓል ነው፡፡

ፍቼ ጫምባላላ
ሲዳማ ብሔር የራሱ የሆነ የዘመን መቁጠርያ ስርዓት ያለው ሲሆን ይህም በዚህም የዘመን መቁጠርያ መነሻነት የሚከበረው የዘመን መለወጫ በዓል ፍቼ ጫምባላላ የሚባል ሲሆን በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፡፡ የሲዳማ ብሔር የራሱ የሆነ የቀን መቁጠርያ ስርዓት ያለዉ ሲሆን በሳምንቱ ዉስጥ ያሉ ቀናት "ቃዋዶ ፤ቃዋላንካ፤ ዲኮ፤ ዴላ" በመባል ይታወቃሉ፡፡
የፍቼ በዓል ቀን ከሁለት ሳምንት በፊት ቀደም ብለዉ ወማዎች(የሀይማኖት አባቶች) የጎሳ መሪዎች(ሞቴ) ጭሜሳዎች (ሽማግሌዎች) ኡሱራ(ጾም) ይይዛሉ፡፡ በዚህም ጾም ሁሉም አይነት ምግብ ይጾማሉ፡፡ የፍቼ ቀን ሊደርስ አራት ቀን ቀርቶ እያለ መሰረት የመጣል (ሣፎ) ቄጣላ ‹‹አዲቻ›› በመባል የሚታወቀዉን የቄጣላ አይነት ወጣቶች ይጨፍራሉ፡፡ ሌላዉ ለፍቼ በዓል የሚደረገዉ ዝግጅት አባቶች ለልጆቻቸዉ አዲስ ልብስ መግዛት ለከብቶቻቸዉ ሳር (ካሎ) መከለል ቦሌ(ጨዋማ አፈር) ያዘጋጃሉ፡፡ በፍቼ ዕለት አመሻሽ ሁሉም በየደጃፉ ሁሉቃ (በእርጥብ እንጨት የሚዘጋጅ መሻሎክያ) አዘጋጅተዉ ሁሉም የበተሰብ አባላት ከነከብቶቻቸዉ ይሾልካሉ ይህም ስርዓት የሚያመለክተዉ ከአሮገዉ ዓመት ወደ አዲሱ ዓመት በሰላም መሻገራቸዉን ነዉ፡፡ በፍቼ ምሽት ሥጋ አይበላም ምክንያቱም ብሔረሰቡ በዓሉ የከብቶቻቸዉም በዓል እንደሆነ ስለምያምኑ ነዉ፡፡በፍቼ ዕለት ከእንሰት የሚሰራውና ተወዳጅ የሆነው ምግብ ቡሪሳሜ በሻፌታ ይቀርባል፡፡
ከዛ ቦኀላ በአንድ ላይ እየበሉ በታላቅ ሽማግሌ ቤት ጀምረዉ ሌሊቱን እስከ 10፡00 ሰዓት ድረስ ከቤት ወደ ቤት እየዞሩ እየበሉና ወተት እየጠጡ በደስታና በፈንጠዚያ ያሳልፋሉ፡፡ ተበልቶ ገበታዉ ከመነሳቱ በፊት አራት ጊዜ ፍቼ ጄጂ (ፍቼ ለዘላለም ትኑር) ብለዉ መልካም ምኞታቸዉን ይገልጻሉ፡፡
ጫምባላላ
በፍቼ ማግስት ልጆች በሰፈሩ እየዞሩ አይዴ ጫምባላላ እያሉ ይሄዳሉ፡፡ የአባባሉ ትርጉም እንካን ለጫምባላላ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ማለት ነዉ፡፡ ከቤት ዉስጥ ያሉ ኢሌ! ኢሌ! ብለዉ ይቀበላሉ፡፡ ትርጉሙ እንኳን አብሮ አደረሰን ማለት ነዉ፡፡ እንደዚህ ካሉአቸዉ በኋላ ወደ ቤት ይገቡና ቡሪሳሜ በእርጎ ተሰቶአቸዉ ይመገባሉ፡፡ እንደዚህ እየሆኑ ሰፈሩን ይዞራሉ፡፡ በዚህ ቀን አባቶች ለከብቶቻቸዉ ተከልሎ የተዘጋጀ ሳር ዉስጥ ቦሌ ነስንሰዉ እያበሉ ይዉላሉ፡፡
ከብቶቹ ከጠገቡ በኋላ ግን ከ10 ሰዓት ጀምሮ በቄጣላ ወደ ጉዱማሌ ይሄዳሉ፡፡ ከፍቼ ቀን ቀጥሎ ከቀጣዩ የቃዋዶ ቀን ጀምሮ በአባቶች የሚዜም ክዋኔ ”ፍቼ ፉሎ” (ግልቤቴ ቄጣላ) በመባል የሚታወቀው ህዝባዊ የበዓል አከባበር ይካሄዳል፡፡
ግልቤ ትርጉሙ ብዙ (በብዙ ቁጥር) ማለት ሲሆን ቄጣላ ማለት ደግሞ በበቁ አባቶች የሚዜም ባህላዊ ክዋኔ ነው፡፡ ይህንን ስርዓት በጎሳ መሪዎች ወይም (ሞቴ) እየተመሩ የጎሳ አባላት በተለይ ወንዶች ጎንፋና ሴማ (ባህላዊ አልባሳት) ለብሰው በረድፍ በረድፍ ቄጣላ እየረገጡ ወደ ማክበርያ ስፍራ የሄዳሉ፡፡

ሞቴዎች በበዓሉ ፍጻሜ ዕለት ለህዝቡ በዓመቱ ውስጥ ማድረግ የሚገባቸውን በማስመልከት ምክር መስጠት የጀምራሉ፡፡ በዚህ ረገድ ትኩረት የሚያደርጉት ለአገር ሰላምና ሁሉም በስራ ራሱንና ሀገሩን እንዲጠቅም መክረው በምርቃት የበዓሉ ፍጻሜ እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡
በየገበያ ቀን ቄጣላው እያነሰ እያነሰ ይሄድና አንድ ወር ሲሆን የአመቱ የፍቼ ጫምበላላ በዓል አከባበር ፍጻሜ ይሆናል፡፡ ይህ ስርዓት ከክልሉ አልፎ የአለም ቅርስ በመሆን በዩኔስኮ በመመዝገብ የብዙ ጎብኝዎች ቀልብ ሳቢ ስርዓት ሆኗል፡፡
የሲዳማ ብሔር ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት
ከጥንት ጀምሮ ሲዳማ ብሔር የመንግስት አስተዳደር ጽንሰ ሀሳብ ባልነበረበት ጊዜ የራሱ የሆነ አስተዳደር የነበረውና ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቹ መፍትሔ ለማግኘት በራሱ የግጭት አፈታትና ባህላዊ የዳኝነት ስርዓትን ሲያካሂድ ቆይተል፡፡ የሲዳማ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት ያለው ጉልህ ሚና ለችግሮች መፍትሔ መስጠት መቻሉ ብቻ ሳየሆን በብሔረሰቡ ዲሞክራሲያዊ እሴቶች ያሉት መሆኑ ነው፡፡ የሲዳማ ብሔር በውስጡ በርካታ ጎሳዎች ያሉት ሲሆን በእያንዳንዱ ጎሳ የጎሳ መሪዎችና በዕድሜ የገፉ አረጋውያን የመሪነት ሚና አላቸው ፡፡
አንዳንድ ጊዜ ስለዳኝነቱ ለመማር ወጣት ወንዶች ችሎቱን በራሳቸው ተነሳሽነት በመቀላቀል ልምድ ለማግኘት ይጠቀሙታል፡፡ የባህላዊ ዳኝነት ስርዓቱ በርካታ ዲሞክራሲያዊ ገጽታዎች ያሉት ሲሆን በዋናነትም ”የአፊኒ” ስርዓት አንዱ ነው፡፡ አፊኒ ማለት ጥሬ ትርጉሙ ሰማችሁ በሚል ሀሳብን ለማንሸራሸር እና ለማሰባሰብ የሚረዳ የንግግር ዘይቤ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በመሆኑም አፊኒ እውነትን (ሀላሌን) ከመፈለግ ቂም በቀልን ከመሻር ከፍትህ አሰጣጥ ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ስርዓት ሲሆን ይህን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ጥረቶች በመደረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

ባህላዊ ምግብ ቤቶች በሀዋሳ
በሐዋሳ ከተማ እንግዶችን ሊያስተናግዱ የሚችሉ ከ25 በላይ የሲዳማ ባህላዊ ምግብ ቤቶች የሚገኙ እነዚህ ምግብ ቤቶች/ሆቴሎች የተለያዩ ጣፋጭ የሲዳማ ባህላዊ ምግቦች የሚያዘጋጁ ሲሆን በሆቴሎቹ የሚዘጋጁ ምግቦች ከእንሰት፣ ከበቆሎና ከገብስ ሲሆን እነኚህም እነደ ቡሪሳሜ፣ ጩካሜ፣ ኮፋሜ፤ ኦሞልቾ፤ ዱዋሜ፤ ጫንጫናሜ የመሳሰሉት በመሀከለኛና ደረጃቸዉን በጠበቁ አለም አቀፍ ሆቴሎች በማቅረብ ለባህላዊ ምግብ እድገትና የብሔሩን የተለያዩ ባህላዊ ሀብቶች መታወቅ የራሳቸውን ጉልህ ሚና እየተወጡ ይገኛሉ፡፡
ወደ ከተማችን የሚመጡ እንግዶች የከተማዋን ውብ መዳረሻዎች ከመጎብኘት ባለፈ እነዚህን ጣፋጭና ተወዳጅ ባህላዊ ምግቦች በመመገብ የሚኖራቸውን ቆይታ ያማረ ስለማድረጋቸው በአንደበታቸው የሚመሰክሩት ነው፡፡


ባህላዊ አልባሳት
ሌላው በሀዋሳ ከተማ ባህላዊ አልባሳትን አዘጋጅተዉ ለገቢያ የሚያቀርቡ ማህበራትና ግለሰቦች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም በባህል ልብስ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ለከተማዉ ባህላዊ አልባሳትና ለቱሪዝም ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡
ማህበራቱ የሲዳማን ቱባ ባህል የሚያንፀባርቁና የተለያዩ ብሄር ብሄረቦች አልባሳትን በማዘጋጀት ባህልን ከማስተዋወቅ አልፈዉ ለከተማዉ ገቢ ዕድገትና በስራ ዕድል ፈጠራ የራሳቸውን አሻራ እያኖሩ ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ ተቋማት የሚዘጋጁ የሲዳማ ባህላዊ አልባሳትን ለመጠቀስ ያክልም ጎንፋ፣ ጎርፋ፣ ቆሎ፣ ወዳሬ እና ላሴ የሚባሉ ሲሆን አልባሳቱ የቱሪስቶችን ቀልብ በመሳብ በጎብኝዎች እና በከተማዋ ነዋሪዎች ልዩ ትኩረት ማግኘት የቻሉም ናቸው፡፡ ይህ ዘርፍ የባህል ቱሪዝምን ከማሳደግ ባለፈ ለብዙ ወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ለከተማዉ ወጣቶች ኢኮኖማዊ ተጠቃሚነት ሚናዉን እየተወጣ ይገኛል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጎብኝዎች ወደ ሀዋሳ ሲመጡ እነዚህን ባህላዊ አልባሳት ገዝተው ሲደምቁ መመልከት እየተለመደ መጥቷል፡፡

ባህላዊ የቀርከሃ ስራ
በሀዋሳ ከተማ ከ4 በላይ በባህላዊ ቀርከሃ ስራ የተሰማሩ ማህበራት ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ማህበራት ለከተማው ባህላዊ ቱሪዝም እድገት ከፍተኛ አስተዋጸ እያበረከቱ ይገኛል፡፡ ማህበራቱ የተለያዩ ባህላዊ አልጋዎችን፤ የሲዳማ ባህላዊ የደጋ አከባቢ ቤቶች (ሼካ ቤት)፤ በማዘጋጀት ከከተማው ማህበረሰብ አልፎ ለቱሪስቶች ሳቢ መሆን የቻሉም ናቸው፡፡ ይህ የማህበራቱ ክህሎት አሁን ላይ ከከተማዉ አልፎ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡

የሀዋሳ ከተማ ባህል ኪነት ቡድን
የሀዋሳ ከተማ ባህል ኪነት ቡድን የተመሰረተው በ2004 ዓ.ም ሲሆን የቡድኑ አባላት 22 ናቸዉ፡፡ ኪነት ቡድኑ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የሲዳማንና የተለያዩ ብሄሮች ሙዚቃዎች እያስተዋወቀና ታዳሚዎችን እያዝናና የቆየ ሲሆን ለከተማዉ የባህል ሙዚቃ ዕድገት የራሱን አበርክቶ እያደረገ ይገኛል፡፡ ኪነት ቡድኑ በሲዳማና በሌሎች ባህላዊ ሙዚቃዎችና ስነ-ጥበባዊ ክዋኔዎች ልምዱን እያዳበረ ለጉብኝት ወደ ከተማችን ለሚመጡ እንግዶች ከማዝናናት አልፎ የብሔሩን ባህላዊ ጭፈራዎችና አለባበሶችን እያስተዋወቀ ይገኛል፡፡ የኪነት ቡድኑ የሲዳማ ብሄር ቱባ ባህሎች ማለትም ፋሮ፤ ሃኖ፤ ሆሬ፤ ቄጣላና ሌሎች ባህላዊ ውዝዋዜዎችን ለጎብኝዎችና ታዳሚዎች በማስተዋወቅም ነው ሚናውን እየተወጣ የሚገኘው፡፡
ለ/ የትራንስፖርትና መገናኛ ዘርፍ፣- እንደ ወደቦች እና አየር ማረፊያዎች ያሉ የመጓጓዣ ዘዴዎችን እና የመጓጓዣ እና የጉዞ መሠረተ ልማትን የሚያካትት ተለዋዋጭ የቱሪዝም አካልን ይፈጥራል። ይህ ዘርፍ ጥራት ያለው፣ አስተማማንነትና ምቾት ያለው ልዩነትን የሚፈጥር በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎቶችን የሚሰጥ እንዲሆን የሚጠበቅ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ሀዋሳ በምን ደረጃ ላይ ትገኛለች?
ሀዋሳ የአይርም የየብስም በርካታ የትራንስፖርት አማራጮች ያላት ከተማ ነች፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ ሀዋሳ እንዲሁም ከሀዋሳ ወደ አዲስ አበባ ለሚደረጉ ጉዞዎች የ-- ኤየር ፖርትን ጨምሮ በየብስ የተለያዩ አገር አቋራጭ አውቶቡሶች፣ መከከለኛ የመያዝ አቅም ያላቸው ዘመናዊ የሰው ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች በተከታታይ አገልግሎት የሚገኝበት እውነታ ነው ያለው፡፡
ከከተማዋ ወደ ሌሎቹም የሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አካባቢዎች እንዲሁም ሌሎች የደቡብና የደቡብ ምእራብ አካባቢዎች ለሚደረጉ ጉዞዎች በየእለቱ እጅግ በርካታ የሆኑ የሕዝብና የግል ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች አገልግሎቶችን ይሠጣሉ፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም የቱር ጋይድ የኪራይ መኪናዎች በስፋት ይገኛሉ፡፡
በከተማዋና በዙሪያዋ ለሚደረጉ የቱሪስት እንቀስቃሴዎች በሀዋሳ ኃይቅ ላይ ለመዝናናት የተለያዩ ምቾትና የተለያየ የመያዝ አቅም ያላቸው በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ጀልባዎች ይገኛሉ፡፡ በከተማው ውስጥ ለሚደረግ እንቅስቃሴ የከተማ አውቶቡሶች፣ ላዳዎች፣ ሚኒባሶች፣ ኪውትስና ዳማስ መኪናዎች፣ ባለሶስት እግር ባጃጆችን ወዘተ… መጠቀም ይቻላል፡፡
ሐ/ የመስተንግዶ ዘርፍ፣- ይሕ ዘርፍ የመስተንግዶ አደረጃጀት፣ የምግብ አቅርቦት ድርጅት እና የህብረተሰቡ ለቱሪስቶች እና ቱሪዝም ንግድ ያላቸው አመለካከት የሚመለከት ሲሆን እንደ ማረፊያ ንዑስ ክፍል (መስተንግዶ)፣ የምግብ አገልግሎት ንዑስ ክፍል (ምግብ) እና መዝናኛ ባሉ ንዑስ ዘርፎች የተከፋፈለ ነው። ከታች እንደሚታየው ይህ ዘርፍ ከማረፊያች አንጻር ሆቴሎችን፣ አፓርትመንቶችን፣ ካምፖችን፣ ሎጆችን፣ ቪላዎችን፣ ሪዞርቶችን፣ ማረፊያ ቤቶችን፣ ወዘተ… ሲያካትት በምግብ አገልግሎት ንዑስ ዘርፍ ፈጣን የምግብ ኦፕሬተሮችን፣ የሽያጭ መሸጫ ቦታዎችን፣ ሬስቶራንቶችን፣ የምግብ አቅርቦት/ተቋማዊ ምግብን ወዘተ ያጠቃልላል። ከዚህ አንጻር ሀዋሳ ከተማን ስንቃኝ እጅግ በርካታ ሆቴሎች፣ እንግዳ ማረፊያ በቤቶች፤ሪዞርቶች ወዘተ.. የሚገኙባት ሲሆን ከዚህ ስር ከተገለጹት በተጨማሪ ሙሉ ዝርዝሩን ሆቴሎች በሚለው ማቀፊያ ውስጥ ይመልከቱ፡፡