ሀዋሳ ስትመሰረት ለቱሪዝም እድገትና ልማት የሚመች የተፈጥሮ አቀማመጥና ገጽታዎችም እንዳላት ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡ ከተማዋ ስያሜዋን ያገኝበት የሐዋሳ ኃይቅ በዚህ ጉዳይ ቅድሚያውን ይይዛል፡፡ ሀይቁ በውስጡ የተለያዩ አሳዎችንና ሌሎች ብዝሀ ህይወቶች የያዘ ሲሆን የከተማዋን የአየር ንብረት ነፋሻማና ለሰዎች ምቹ እንዲሆን አድረጓል፡፡ በሀይቁ ውስጥና በዳርቻዎች ባሉ ስፍራዎች የተለያዩ ቀልብን የሚስቡ አእዋፋትና የዱር እንስሳት ጉማሬን ጨምሮ ይገኛሉ፡፡ ከሀዋሳ ከተማ ኃይቅ ጋር በተገናኘ የብዙዎችን ቀልብ የሚስበው በሀዋሳ ኃይቅ ዳርቻዎች የሚከናወኑ አሳን ማእከል ያደረጉ የምግብና የመጠጥ ትእይንቶች ናቸው፡፡ በዚህ ጉዳይ በተለምዶ አሞራ ገደል በሚባለው አካባቢ የሚደረግ የአሳ ማህበረሰብ አስገራሚ የእለት ተእለት መስተጋብር ነው፡፡ የአሳ ሾርባ፣ የአሳ ጥሬ ስጋ ወዘተ… በአካባቢው ከሚዘጋጁ መባያዎችና ማጣፈጫዎች ጋር እየቀረቡ ሰዎች ሲመገቡ ማየት እጅጉን ቀልብ ይስባል፡፡ እዛው ጋር ዘመናዊ ጀልባዎችን እየተጠቀሙ በኃይቁ የተለያዩ አቅጣጫዎች እየተጓዙ መዝናናት በጣም ግሩም ቆይታን ያጎናጽፋል፡፡ በጥቅሉ በሀዋሳ ኃይቅ ዙሪያ ብቻ መቆየት ብቻውን ሙሉ ተዝናኖት ለማግኘት ያስችላል ብሎ ደፍሮ መናገር ያስችላል፡፡
ሀዋሳ ከአየር ንብረቷና የተፈጥሮ አቀማመጧ ምቹነት በተጨማሪ በዙሪዋ የሚገኙ ተራሮችና ረግራጋማ አካባቢዎችም ለቱሪዝም እጅግ ከፍተኛና ሰፊ አማራጮችን ይዘው የሚገኙ ናቸው፡፡ የታቦርና አላሙራ ተራራዎች፣ ኩዩዋታ ኮረብታ፣ የጨለለቃ ረግረጋማ ቦታዎች፣ ቡርቂቶና የወንዶ ገነት ፍልውሀዎች በሀዋሳና በአቅራቢያዋ እንዲሁም በሲዳማ ክልል ውስጥ የሚገኙ ምርጥ ገጸ-ምድራዊ በረከቶችና አቀማመጦች፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሀብቶች ለአብነት የሚጠቀሱ የቱሪስት መዳራሻዎች ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከተማዋ እጅግ ዘመናዊ የሆቴሎችና ሌሎችም አገልግሎቶች የሚሰጥባት ከመሆኗም በላይ ቱሪስቱን የሚመሩና ሁኔታዎችን የሚያመቻቹ የተደራጁ የቱሪስት አስጎብኝዎች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል፡፡
ሌላው ከሀዋሳ ከተማ የቱሪስት መስህቦች መካከል የሚነሱት ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ሲሆኑ የከተማውን ብሎም የክልሉን ህዝብ ታሪክና እድገት የሚያስረዱ ባህላዊ ቁሳቁሶች ለጎብኝዎች ቅርብ እንዲሆኑ በከተማ የባህል ሙዚየም እንዲገኙ ተደርጓል፡፡ ከተማዋ ትላልቅ ሁነቶችን የማስተናገድ አቅሟ ከፍተኛ ከመሆኑም ጎን ለጎን በተለይ በህክምና ቱሪዝም ዘርፍም በስፋት ትታወቃለች፡፡ የሎቄ ቤተመንግስትን ጨምሮ የሚጎበኙ ታሪካዊ ቦታዎችም እንዳሉ ማንሳት ይቻላል፡፡
ሀዋሳ በስፖርቱም መስክ በተለያዩ ስፖርታዊ እንቅሰቃሴዎችን የእግር ኳስ፣ አትሌቲክስ ብሎም ባህላዊ ስፖርታዊ ውድድሮችን ማስተናገድ የሚችል ሁሉ አቀፍ አቅሞች ያላት ከተማም ነች፡፡
በዚሁም መሰረት ወደ ከተማችን ለጉብኝትና ለተለያዩ ተያያዥ ጉዳዎች ሀዋሳን መረዳት ለምትፈልጉ ወገኖቻችን ወቅታዊና የተሟላ የቱረዝም መረጃ በዘመናዊ መንገድ በያላችሁበት ታገኙ ዘንድ ይህን የተቋማችን ድህረ-ገጽ አቅርበንላችኋል፡፡ በመጨረሻም ከተማችን በሁሉም ረገድ በቀጠናው ምርጥ የቱሪዝም ብሎም የንግድና የኢንቨስትመንት መዳረሻ ስለሆነች በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ስም ሀዋሳ መጥተው ምርጥ ግዜዎን እንዲያሳልፉ አለፍ ሲልም ኢንቨስት እንዲያደርጉ እጋብዛለሁ፡፡